ከክቡር ቁርኣን የዒሳ (ዓለይሂ ሰላም) ታሪክ
አዘጋጅ፦ ፋቲን ሰብሪ
ትርጉም፦ መ. ሉአይ ሰብሪ
2018
የመጀመሪያ ዕትም
1- መቅድም
ምስጋና ሁሉ ለአላህ [1] ብቻ የተገባ ነው፤ ተገቢው ሹክርም ለእርሱው ነው፤ እርዳታውን እንጠይቃለን፤ ምህረቱንም እንማፀነዋለን፤ ከኃጢአታችንም ከመጥፎ ሥራዎቻችንም ወደ እርሱው በንሰሀ እንመለሳለን።
[1] ሙስሊሞች፣ አይሁዶች እና በምስራቃዊ ዐረቢያ ዙርያ ያሉ ክርስቲያኖችም “አላህ” የሚለውን ስም የዓለማቱን ጌታ ለማመልከት ይጠቀሙበታል። “አላህ” የሚለው ስም በብሉይ ኪዳን 89 ጊዜ ተጠቅሷል (ዘፍጥረት 2፡4 ፤ መጽሐፈ ዳንኤል 6:20፤ የዐረብኛውን እና የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ ይመልከቱ)።
ከአላህ በቀር ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለና አጋር የሌለው ብቸኛ አምላክ መሆኑንም እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የእርሱ አገልጋይ ባሪያና መልክተኛ መሆናቸውንም እመሰክራለሁ። የመርየም ልጅ ዒሳ የአላህ ባሪያና መልዕክተኛ መሆናቸውንም እመሰክራለሁ።
ይህ መጽሐፍ የዒሳ ዓለይሂ ሰላምን ተልዕኮ መሰረቶችን ቀለል ባለ መልኩ የሚገልፅ ጥቅል ማብራርያ ነው። ይሀውም በአላህ ማመን እና እርሱን በብቸኝነት ማምለክ ነው። እንዲሁም የዒሳ እና የእናቱ መርየም ታሪክም ተካቷል። ይህችን ግልፅ እና ንጹህ እምነትን በተመለከተም መረጃና ማስረጃ ከቁርኣን፣ ከኦሪት እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስም ቀርቧል።
ይህ መጽሐፍ እውነትን ለሚሹ እና ብሩህ አእምሮ ላላቸው ሰዎች፡ የዓለማቱ ጌታ በየትኛውም የታሪክ ዘመናት ለነበሩ ሕዝቦች ሁሉ በመልዕክተኞቹ በኩል የላከው እውነተኛ መልእክቱ አንድ መልዕክት መሆኑን ለመገንዘብ ይረዳቸዋል። ይሀውም ንጹሕ የሆነ የተውሒድ (አላህን በብቸኝነት የማምለክ አሀዳዊ አምልኮ) መልዕክት ነው።
ዒሳ ዓለይሂ ሰላምም ከነዚህ ህዝባቸውን ወደ ንፁሁ አሀዳዊ አምልኮ (ተውሒድ) ለመምራት ከተጣሩ ፈሪሃ ኣላህ ከሆኑ መልዕክተኞች መካክል አንዱ ናቸው። ይሁን እንጅ ብዙዎች ከጎዳናው አፈንግጠው የራሳቸውን ፍላጎት (ስሜት) በመከተላቸው ምክንያት ከሃይማኖታዊ አስተምህሮው ራቁ።
2- የዒሳ ዓለይሂ ሰላም ታሪክ የሚጀምረው የዒምራን ሚስት (የማርያም እናት) ለዓለማቱ ጌታ ከገባችው ስለት ነው፦
(ቁርኣን [2] ምዕራፍ 3: 33-37)
(2) ቁርኣን የዓለማት ጌታ ከላካቸው መጻሕፍት መካከል የመጨረሻው ነው። ሙስሊሞች ከቁርኣን በፊት በተላኩትም መጽሐፍት ሁሉ (በኢብራሂም ሱሑፍ፣ በመዝሙረ ዳዊት (ዘቡር)፣ በኦሪት (ተውራት) እና በወንጌል (ኢንጂል)... እንዲሁም በሌሎችም) የሚያምኑ እንደመሆናቸው መጠን የመጻሕፍቱ ሁሉ እውነተኛው መልዕክት በሆነው ንጹሕ አሀዳዊ አምልኮ (በአላህ ማመን እና እርሱን በአምልኮ ብቸኛ ማድረግ እንደሆነም) የሚያምኑ ናቸው። ይሁን እንጅ ከቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት በተለየ መልኩ ቁርኣን አንዱን ከሌላው ነጥሎ በሆነ በአንድ የተወሰነ ቡድን ወይም ክፍል ብቻ ነጥሎ የተገደበ አይደለም። ቁርኣን ለሁሉም ሙስሊም ተመሳሳይ የሆነ አንድ አይነት እንጅ የተለያየ ቅጂ የለውም፤ ምንም ዓይነት ለውጥም አልተደረገበትም። ቁርኣን በሁሉም ሙስሊሞች ዘንድ የሚዘዋወር በሰላት ውስጥም የሚያነቡት፤ ለሁሉም የሕይወት ጉዳያቸውም መመለሻቸው ነው። በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች ቁርኣንን በነብዩ ሙሐመድ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለምና በባልደረቦቻቸው ዘመን ሲነበብ በነበረው አኳኋን ምንም ዓይነት ፊደል ሳይቀይሩ፣ ሳይሰርዙና ሳይበርዙ የሚያነቡት ነው። የዓለማቱ ጌታ ዐረቦችንመ ይሁን ዐረብ ያልሆኑትንም ቁርኣንን የመሰለ ይዘው እንዲመጡ ውርርድ አቅርቦላቸዋል፤ (ይህንንም ፈተና ያቀረበው) በጊዜው የነበሩት ዐረቦች በአንደበተ ርቱዕነት፣ በንግግር እና በግጥም ችሎታ ከሌላውም በላይ እጅግ የተካኑ መሆናቸው የታወቀ ከመሆኑም ጋር ነው። ይሁን እንጅ በዚህ የአገላለፅ ስልቱ እነርሱም ቢሆኑ ይህ ቁርኣን ከአላህ ውጪ ከማንም ሊሆን እንደማይችል እርግጠኛ የሆኑበት ጉዳይ ነበር።
"አላህ አደምን፣ ኑሕንም፣ የኢብራሂምንም ቤተሰብ፣ የዒምራንንም ቤተሰብ በዓለማት ላይ መረጠ። (33) ከፊልዋ ከከፊሉ የሆነች ዝርያ አድርጎ (መረጣት)። አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው። (34) የዒምራን ባለቤት (ሐና) «ጌታዬ ሆይ! እኔ በሆዴ ውስጥ ያለውን (ፅንስ ከሥራ) ነጻ የተደረገ ሲኾን ለአንተ ተሳልኩ። ከእኔም ተቀበል አንተ ሰሚው ዐዋቂው ነህና» ባለች ጊዜ (አስታውስ)። (35) በወለደቻትም ጊዜ፡- «ጌታዬ ሆይ! እኔ ሴት ሆና ወለድኋት።» አላህም የወለደችውን ዐዋቂ ነው። «ወንድም እንደ ሴት አይደለም። እኔም መርየም ብዬ ስም አወጣሁላት። እኔም እስዋንም ዝርያዋንም ከተረገመው ሰይጣን በአንተ እጠብቃቸዋለሁ» አለች። (36) ጌታዋም በደህና አቀባበል ተቀበላት። በመልካም አስተዳደግም አፋፋት። ዘከሪያም አሳደጋት፤ ዘከሪያ በርሷ ላይ በምኹራቧ በገባ ቁጥር እርስዋ ዘንድ ሲሳይን አገኘ። «መርየም ሆይ! ይህ ለአንቺ ከየት ነው» አላት። «እርሱ ከአላህ ዘንድ ነው። አላህ ለሚሻው ሰው ሲሳዩን ያለ ድካም ይሰጣል» አለችው። (37)"
3- የድንግል መርየም ደረጃ እና ብስራቱ፦
(ቁርኣን ምዕራፍ 3: 42-47)
"መላእክትም ያሉትን (አስታውስ)። «መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ። አነጻሽም። በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሽ። (42) መርየም ሆይ! ለጌታሽ ታዘዢ። ስገጂም። ከአጎንባሾቹም ጋር አጎንብሺ። (43) ይህ ወደ አንተ የምናወርደው የሆነ ከሩቅ ወሬዎች ነው። መርየምንም ማን እንደሚያሳድግ ብዕሮቻቸውን (ለዕጣ) በጣሉ ጊዜ እነሱ ዘንድ አልነበርክም። በሚከራከሩም ጊዜ እነሱ ዘንድ አልነበርክም። (44) መላእክት ያሉትን (አስታውስ)፡- «መርየም ሆይ! አላህ ከርሱ በሆነው ቃል ስሙ አልመሲሕ ዒሳ የመርየም ልጅ በዚህ ዓለምና በመጨረሻውም ዓለም የተከበረ ከባለሟሎችም በሆነ (ልጅ) ያበስርሻል። (45) በሕፃንነቱና በከፈኒሳነቱ ሰዎቹን ያነጋግራል። ከመልካሞቹም ነው። (አላት)። (46) ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስሆን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል አለች። ነገሩ እንዳልሽው ነው። አላህ የሚሻውን ይፈጥራል። አንዳችን በሻ ጊዜ ለርሱ ሁን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይሆናል አላት። (47)
4- የእርግዝናዋ ተአምር እና የኢየሱስ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) ውልደት፡-
(ቁርኣን ምዕራፍ 19: 16-35)
"በመጽሐፉ ውስጥ መርየምንም ከቤተሰቧ ወደ ምሥራቃዊ ስፍራ በተለይች ጊዜ (የሆነውን ታሪኳን) አውሳ። (16) ከእነሱም መጋረጃን አደረገች፡፡ መንፈሳችንምም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን [3]። ለእርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት። (17) «እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ። ጌታህን ፈሪ እንደ ሆንክ (አትቅረበኝ)» አለች። (18) «እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ» አላት። (19) «(በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ሆኜ አመንዝራም ሳልሆን ለእኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል!» አለች። (20) አላት «(ነገሩ) እንደዚህሽ ነው።» ጌታሽ «እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው። ለሰዎችም ታምር ከእኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው» አለ። (ነፋባትም)። (21) ወዲያውኑም አረገዘችው። በእርሱም (በሆዷ ይዛው) ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች። (22) ምጡም ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት። «ዋ ምኞቴ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ። ተረስቼም የቀረሁ በሆንኩ» አለች። (23) ከበታቿም እንዲህ ሲል ጠራት «አትዘኝ። ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል። (24) «የዘምባባይቱንም ግንድ ወዳንቺ ወዝውዣት ባንቺ ላይ የበሰለን የተምር እሸት ታረግፍልሻለችና። (25) «ብይም፣ ጠጭም፣ ተደሰችም። እኔ ለአልረሕማን ዝምታን ተስያለሁ፤ ዛሬም ሰውን በፍጹም አላነጋግርም» በይ። (26) በእርሱም የተሸከመችው ሆና ወደ ዘመዶቿ መጣች። «መርየም ሆይ! ከባድን ነገር በእርግጥ ሠራሽ» አሏት። (27) «የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም። እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም» አሏት። (28) ወደርሱም ጠቀሰች። «በአንቀልባ ያለን ሕጻን እንዴት እናናግራለን!» አሉ። (29) (ሕፃኑም) አለ «እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፡፡ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል።» (30) «በየትም ስፍራ ብሆን ብሩክ አድርጎኛል። በሕይወትም እስካለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንም በመስጠት አዞኛል።» (31) «ለእናቴም ታዛዥ (አድርጎኛል)። ትዕቢተኛ እምቢተኛም አላደረገኝም። (32) «ሰላምም በእኔ ላይ ነው፡፡ በተወለድሁ ቀን፣ በምሞትበትም ቀን፣ ሕያው ሆኜ በምቀሰቀስበትም ቀን።» (33) ይህ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው። ያ በርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው። (34) ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባውም። (ከጉድለት ሁሉ) ጠራ። ነገርን በሻ ጊዜ ለርሱ የሚለው «ሁን» ነው ወዲያውም ይሆናል። (35)"
[3] የዓለማት ጌታ በብዙ የክቡር ቁርኣን አንቀጾች ራሱን ለመግለጽ "እኛ" የሚለውን ቃል መጠቀሙ በዐረብኛ ቋንቋ ኃያልነትን እና ታላቅነትን የሚገልፅ ነው። በእንግሊዝኛ (በአማርኛ) ቋንቋም ቢሆን እንዲሁ "እኛ መንግስት" እየተባለ የሚገለፅ ሲሆን ብዙ ቁጥር የሚጠቁምን ተውላጠ ስም ከፍ ያለ ቦታ ላይ ያለ (እንደ ንጉስ፣ንጉሠ ነገሥት ወይም ሱልጣን) ግለሰብንም ለማመልከት ያገለግላል። ይሁን እንጅ ቁርኣን ከአምልኮ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮችን ሲገልፅ የአላህን አንድነት ነው ሁል ጊዜ አበክሮ የሚገልፀው።
5- የዒሳ ዓለይሂ ሰላም ነቢይነት እና ተአምራቶቻቸው፡-
(ቁርኣን ምዕራፍ 5: 75-76)
"የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም። እናቱም በጣም እውነተኛ ናት። (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ፤ አንቀጾችን ለነርሱ (ለከሓዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት ከዚያም (ከእውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት። (75) «ከአላህ ሌላ ለእናንተ መጉዳትንና መጥቀምን የማይችልን ትገዛላችሁን» በላቸው። አላህም እርሱ ሰሚው ዐዋቂ ነው። (76)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 3: 48-50)
"ጽሕፈትንና ጥበብንም ተውራትንና ኢንጂልንም ያስተምረዋል። (48) ወደ እስራኤልም ልጆች መልክተኛ ያደርገዋል። (ይላልም)፡- «እኔ ከጌታዬ ዘንድ በተዓምር ወደ እናንተ መጣሁ። እኔ ለናንተ ከጭቃ እንደ ወፍ ቅርፅ እፈጥራለሁ። በርሱም እተነፍስበታለሁ። በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕውር ሆኖ የተወለደን፣ ለምጸኛንም አድናለሁ። ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ። የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ውስጥ በእርግጥ ተዓምር አለበት።» (49) «ከተውራትም ከእኔ በፊት ያለውን ያረጋገጥሁ ስሆን የዚያንም በእናንተ ላይ እርም የተደረገውን ከፊል ለእናንተ እፈቅድ ዘንድ (መጣኋችሁ) ከጌታችሁም በሆነ ታምር መጣሁዋችሁ። አላህንም ፍሩ፤ ታዘዙኝም።» (50)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 5: 112-115)
"ሐዋርያት፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! ጌታህ በእኛ ላይ ከሰማይ ማእድን ሊያወርድልን ይችላልን» ባሉ ጊዜ (አስታውስ)። «ምእመናን እንደ ሆናችሁ አላህን ፍሩ» አላቸው። (112) «ከእርሷ ልንበላ ልቦቻችንም ሊረኩ እውነት ያልከንም መሆንህን ልናውቅና በእርሷም ላይ ከመስካሪዎች ልንሆን እንፈልጋለን» አሉ። (113) የመርየም ልጅ ዒሳ አለ፡- «ጌታችን አላህ ሆይ! ለእኛ ለመጀመሪያዎቻችንና ለመጨረሻዎቻችን ባዕል (መደሰቻ) የምትሆንን ከአንተም ተአምር የሆነችን ማእድ ከሰማይ በእኛ ላይ አውርድ። ስጠንም። አንተ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነህና።» (114) አላህ፡- «እኔ (ማእድዋን) በናንተ ላይ አውራጅዋ ነኝ። በኋላም ከእናንተ የሚክድ ሰው እኔ ከዓለማት አንድንም የማልቀጣውን ቅጣት እቀጣዋለሁ» አለ። (115)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 3: 52-53)
"ዒሳ ከነርሱ ክህደት በተሰማውም ጊዜ፡- «ወደ አላህ (ተጨምረው) ረዳቶቼ እነማን ናቸው» አለ፤ ሐዋርያት፡- «እኛ የአላህ ረዳቶች ነን፤ በአላህ አምነናል፤ እኛም ትክክለኛ ታዛዦች መሆናችንን መስክር» አሉ። (52) «ጌታችን ሆይ! ባወረድከው አመንን፤ መልክተኛውንም ተከተልን፤ ከመስካሪዎችም ጋር መዝግበን» (አሉ)። (53)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 61: 14)
"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የመርየም ልጅ ዒሳ ለሐዋርያቶቹ «ወደ አላህ ረዳቴ ማነው?» እንዳለ ሐወርያቶቹም «እኛ የአላህ ረዳቶች ነን» እንዳሉት የአላህ ረዳቶች ሁኑ፡፡ ከእስራኤልም ልጆች አንደኛዋ ጭፍራ አመነች። ሌላይቱም ጭፍራ ካደች። እነዚያን ያመኑትንም በጠላታቸው ላይ አበረታናቸው፤ አሸናፊዎችም ሆኑ። (14)"
6- በዒሳ ዓለይሂ ሰላም ላይ የተደረገ ሴራ እና የዓለማቱ ጌታ አላህ ለእርሳቸው ያደረገው ጥበቃ፦
(ቁርኣን ምዕራፍ 3: 54-59)
"(አይሁዶችም) አደሙ አላህም አድማቸውን መለሰባቸው። አላህም ከአድመኞች ሁሉ በላጭ ነው። (54) አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)። ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ። ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ። ከዚያም መመለሻችሁ ወደእኔ ነው። በርሱ ትለያዩበትም በነበራችሁት ነገር በመካከላችሁ እፈርዳለሁ። (55) እነዚያማ የካዱትን ሰዎች በቅርቢቱ ዓለምና በመጨረሻይቱ ዓለም ብርቱን ቅጣት እቀጣቸዋለሁ፡፡ ለእነርሱም ምንም ረዳቶች የሏቸውም። (56) እነዚያም ያመኑትማ መልካም ሥራዎችንም የሠሩት ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል፡፡ አላህም በዳዮችን አይወድም። (57) ይህ ከተዓምራቶችና ጥበብን ከያዘው ተግሳጽ ሲሆን በአንተ ላይ እናነበዋለን። (58) አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው። ከዐፈር ፈጠረው። ከዚያም ለርሱ (ሰው) «ሁን» አለው፤ ሆነም። (59)"
7- ኢየሱስ ክርስቶስ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አለመሰቀላቸው እና አለመገደላቸው፡-
(ቁርኣን ምዕራፍ 4: 157-159)
"«እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን» በማለታቸውም (ረገምናቸው)፡፡ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡ ግን ለእነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፡፡ እነዚያም በእርሱ ነገር የተለያዩት ከእርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም። (157) ይልቁንስ አላህ (ኢሳን) ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው። (158) ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በእርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም፡፡ በትንሣኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይሆናል። (159)"
8- ተውሒድ (የአላህ ብቸኛ ተመላኪነት) የዒሳ ዓለይሂ ሰላም መሠረታዊ መልዕክት ስለመሆኑ፦
(ቁርኣን ምዕራፍ 3: 51)
"«አላህ ጌታዬና ጌታችሁ ነው፤ ስለዚህ ተገዙት፤ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» (አላቸው)። (51)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 3: 79-80)
"ለማንም ሰው አላህ መጽሐፍንና ጥበብን ነቢይነትንም ሊሰጠውና ከዚያም ለሰዎች «ከአላህ ሌላ ለእኔ ባሮች ሁኑ» ሊል አይገባውም፡፡ «ግን መጽሐፍን የምታስተምሩ በነበራችሁትና የምታጠኑም በነበራችሁት በዕውቀታችሁ ሠሪዎች ሁኑ» (ይላቸዋል)። (79) መላእክትንና ነቢያትንም አማልክቶች አድርጋችሁ እንድትይዙ ሊያዛችሁ (አይገባውም)፡፡ እናንተ ሙስሊሞች ከሆናችሁ በኋላ በክህደት ያዛችኋልን። (80)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 9: 31)
"ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲሆኑ ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፡፡ ከሚያጋሩት ሁሉ የጠራ ነው። (31)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 5: 116-118)
"አላህም፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብላሃልን» በሚለው ጊዜ (አስታውስ)። «ጥራት ይገባህ፤ ለእኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም። ብዬው እንደ ኾነም በእርግጥ ዐውቀኸዋል። በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ። ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም። አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና» ይላል። (116) «በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ ማለትን እንጂ ለነርሱ ሌላ አላልኩም። በውስጣቸውም እስካለሁ ድረስ በነርሱ ላይ ተጣባበቂ ነበርኩ። በተሞላኸኝም ጊዜ (ባነሳኸኝ ጊዜ) አንተ በነሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ። አንተም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነህ።» (117) «ብትቀጣቸው እነርሱ ባሮችህ ናቸው፡፡ ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ» (ይላል)። (118)"
(ቁርኣን ምዕራፍ 4: 171-173)
"እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ። በአላህም ላይ እውነትን እንጅ አትናገሩ። የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ የአላህ መልክተኛ ወደ መርየም የጣላት «የሁን» ቃሉም ከእርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው። በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ። « (አማልክት) ሦስት ናቸው» አትበሉም። ተከልከሉ፤ ለእናንተ የተሻለ ይሆናልና። አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው። ለእርሱ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው። በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው። መመኪያም በአላህ በቃ። (171) አልመሲሕ (ኢየሱስ) ለአላህ ባሪያ ከመሆን ፈጽሞ አይጠየፍም፡፡ ቀራቢዎች የሆኑት መላእክትም (አይጠየፉም)፡፡ እርሱን ከመገዛት የሚጠየፍና የሚኮራም ሰው (አላህ) ሁሉንም ወደ እርሱ በእርግጥ ይሰበስባቸዋል። (172) እነዚያማ ያመኑት መልካሞችንም የሠሩት ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል። ከችሮታውም ይጨምርላቸዋል። እነዚያን የተጠየፉትንና የኮሩትንማ አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል። ከአላህም ሌላ ለእነሱ ዝምድንና ረዳትን አያገኙም። (173)"
9- ስለ ነብዩ ሙሐመድ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም መምጣት በመሲሑ አንደበት ሲበሰር (ሲታወጅ)፡-
(ቁርኣን ምዕራፍ 61: 6)
"የመርየም ልጅ ዒሳም፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በሆነው የማበስር ስሆን ወደእናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በግልጽ ተዓምራቶች በመጣቸውም ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ። (6)"
10 - የማብራሪያ ነጥቦች፦
1.
የዒሳ ዓለይሂ ሰላም ታሪክ የሚጀምረው በማህፀኗ ውስጥ ያለው ልጅ ጌታዋን ሊያመልክ እና በይት አል-መቅዲስን ሊያገለግል ዘንድ በስጦታ እንደምትሰጥ (በመሳል) ይህንንም የዓለማቱ ጌታ አላህ እንዲቀበላት የመርየም እናት ለራሷ በገባችው የስለት ዱዓእ ነው።
2.
የድንግል መርየም ሞግዚትነት ለነቢዩ ዘከሪያ (ዘካርያስ) የተሰጣቸው (ዕጣ ተጣጥለው) የዋስትናዋ ድምጽ ካገኙ በኋላ በመሆኑና ማርያም በይተ'ል-መቅዲስን እንድታገለግል እና ራሷን ለጌታዋ አምልኮ አሳልፋም እንድትሰጥ በእናቷ ስለተሰጠች ይህ ሞግዚትነት እንደ ሃይማኖታዊ ግዴታነት ይቆጠር ነበር።
ነብዩላህ ዘከሪያ ዓለይሂ ሰላም ለአላህ ባላቸው ፈሪሃ አምላክነት የታወቁ ነበሩ። በመሆኑም መርየምን በጠንካራ እምነትና ለዓለማቱ ጌታ ፍጹም (ሙሉ) ታዛዥ እንድትሆን አድርገው ነበር ያሳደጓት።
3.
አላህ ለመርየም አላህን ፈሪ በመሆኗ ከሰጣት ፀጋዎች መካከል አንዱ የእስራኤል ልጆች በችግር ላይ በነበሩበት ወቅት እንኳ ብዙ ሲሳይን የሚለግሳት መሆኑ ነው።
4.
መልአኩ ጂብሪል በሰው አምሳል ወደ እርስዋ በመጣም ጊዜ ከእርሱ እዲከላከልላት ከአላህ ጥበቃ መፈለጓ ለጥብቅነቷና አላህን ፈሪ ለመሆኗ ትልቅ ማሳያ (ማስረጃ) ነው።
5.
መርየም ዒሳ ዓለይሂ ሰላምን በፀነሰች ጊዜ ለጌታዋ ትእዛዝ ሁለመናዋን ሰጠች ከሕዝቧም ተለይታ ርቃ ሄደች።
6.
ምጧን በማቅለል እና ከዘንባባው ግንድ አጠገብ ባለው አስተማማኝ ቦታ ምግብና መጠጥ በማቅረብ እና ከሥሩም የሚፈስ ወንዝንም በማድረጉ የዓለማቱ ጌታ እንክብካቤ እና እዝነት በመርየም ላይ ጎልቶ ታየ።
7.
እመቤት መርየም ያለ አባት ልጅ በመውለድ ታላቅ ወንጀል ፈፀመች ተብሎ በተቀጠፈባትም ጊዜ ጌታዋ አላህ ዝም እንድትል አዘዛትና በአንቀልባ ያለው ሕፃን ዒሳ ዓለይሂ ሰላም እንዲናገርና የእናቱ መርየምንም ንጽህና እርሱ እንዲገልጽ ወሕይ (መለኮታዊ ራዕይ) አወረደለት።
8.
ዒሳ ዓለይሂ ሰላም ነብይነታቸውን፣ የአላህ ባሪያና አገልጋይ መሆናቸውን፣ ለዓለማቱ ጌታ ተገዥ የሆኑ የሰው ልጅ መሆናቸውንና የአላህ መልእክተኛውም መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥተው ገልፀዋል።
9.
ተውሒድ (የአላህ ብቸኛ ተመላኪነት) የዒሳ ዓለይሂ ሰላም መልእክት ውስጥ ዋናው ነጥብ (አስኳል) ነበር። አጋርም ሆነ ልጅ የሌለው አንድና ብቸኛ አምላክ መኖሩንም አረጋግጠዋል። ዒሳ ዓለይሂ ሰላም አላህ በብቸኝነት እንዲመለክም ነበር ጥሪ ያደረጉት።
10.
በዒሳ ዓለይሂ ሰላም በኩል የተፈጸሙ ተአምራት ለዒሳ መልዕክት ውጢታማነት ሲባል በዓለማቱ ጌታ ፍላጎት እና ፈቃድ የተፈፀሙ ነበሩ።
11.
መሲሑ የመጣው የሙሴን መልዕክት እውነተኝነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በመልዕክቱ ውስጥም የተላከኩ ውሸቶችን እና ቅጥፈቶችን ሁሉ ለማስተካከል ነው።
12.
የዓለማቱ ጌታ መልዕክተኛው ዒሳ ዓለይሂ ሰላምን ከስቅላት ባዳናቸውና ወደራሱም ባነሳበት ቅፅበት ተከታዮቻቸው በፍርድ ቀን የበላይ እንደሚሆኑና ጠላቶቻቸውንም ድል እንደሚያደርጉ ቃል ገብቶላቸዋል።
13.
ከዓለማቱ ጌታ አላህ ዘንድ የዒሳ ዓለይሂ ሰላምን ያለ አባት መፍጠር ተአምር ልክ አዳም ያለ አባትና እናት ከዐፈር እንደ መፍጠር ነው።
14.
ዒሳ ዓለይሂ ሰላም አልተገደሉም አልተሰቀሉምም፤ ይልቁኑ አላህ ወደ ራሱ አንስቷቸዋል።
15.
ዒሳ ዓለይሂ ሰላምም ይሁኑ እናታቸው መርየም ከአላህ ውጪ እንዲመለኩ በፍፁም አላዘዙም፤ ይልቁን ሕዝባቸውን የሰዎች ሁሉ ጌታ የሆነውን ፈጣሪ ብቻ እንዲያመልኩ ነው የተጣሩት።
16.
ቁርኣን መርየምና ልጇ ዒሳ ዓለይሂ ሰላም ላይ የተላከከውን የአምላክነት መገለፅ አጥብቆ ተቋውሟል፤ ከዚህ ቅጥፈትም ነፃ አውጥቷቸዋል። ይልቁንም ሁለቱም አላህን በብቸኝነት እንዲመለክ ጥሪ ያደርጉ እንደነበር አስረግጦ ነው የገለፀው።
17.
ዒሳ ዓለይሂ ሰላም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም የተጠቀሰው ለሕዝባቸው የዓለማቱን ጌታ ጥርት አድርጎ ወደ ማምልከ (ወደ ንጹሕ አሐዳዊ አምልኮ) ጥሪ ማድረጋቸው ነው። እንደ ምሳሌ፦
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት:- “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” (ማርቆስ 12: 29-30)
"እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክከውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።" (የዮሐንስ ወንጌል 17: 3)
18.
የነቢዩ ሙሐመድ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም መምጣትን መተንበይ የዒሳ ዓለይሂ ሰላም መልዕክት አካል ነው።
"እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል።" (የዮሐንስ ወንጌል 14: 16)
“እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል።" (የዮሐንስ ወንጌል 15: 26)
11- መደምደሚያ
1. ዒሳ ዓለይሂ ሰላም ይዘውት የመጡት መልእክት የነቢያቱ ሁሉ ተልዕኮ ሲሆን እርሱም ንጹሕ አሐዳዊ አምልኮ ተውሒድ (አላህን በብቸኝነት ጥርት አድርጎ ማምለክ) ነው። ፈጣሪ ሁሉንም መልዕክተኞች ለሁሉም ሕዝቦች ሲልክ በተመሳሳይ ተልዕኮ ነው። በሃይማኖቶች መካከል ያሉ ግልጽ እና ተመሳሳይ የእምነት አስተምህሮዎች አንድ ምንጭ አላቸው እርሱም ፈጣሪ ነው። ልዩነቶች የተፈጠሩት ደግሞ በሰዎች ማዛባት ምክንያት ነው።
2. ፈጣሪ ለፍጥረት የሚያስተላልፈው መልዕክት አንድ፣ ቀላል እና ለመረዳት ገር የሆነ የማያስቸግር እንዲሁም የግድ ከፈጣሪ ጋ በቀጥታ (ያለ ምንም አማላጅ) በማገናኘት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን የታወቀ ጉዳይ ነው።
3. ኢስላም የሚለው ቃል ለዓለማቱ ጌታ ሙሉ በሙሉ ተገዥ መሆን እና እርሱን ያለ አማላጅ ማምለክ ማለት ነው። ይህ መልዕክት በታሪክ ውስጥ የሁሉም መልዕክተኞች መልዕክት ነበር። ብቻውን መመለክ የፈጣሪ መብቱ ነው።
4. በመሰረቱ የሰው ልጅ ሲፈጠር ገና ከፈጣሪው ጋር አምላክነቱንና ጌትነቱን የሚመሰክርበት ቃል ኪዳን ገብቷል። ስለዚህም ነው የፈጣሪ መኖርና ብቸኛ አምላክነት በእያንዳንዱ ሰው ልብ እና ህሊና ውስጥ የተቀበረ ስሜት የሆነው። ይህም አላህ ፍጥረታትን የፈጠረበት ባህሪ እና ተፈጥሮ ነው። ፀሐይ፣ ኮከቡ፣ ተራራው፣ ዛፎች እና አራዊትም ሁሉ ለፈጣሪያቸው ተገዥ የሆኑ በብቸኛ ተመላኪነቱም የሚመሰክሩ ናቸው። (ቁርኣን ምዕራፍ 7 ፡172 ይመልከቱ)
5. በሃይማኖቶች መካከል ያለው ልዩነት የተፈጠረው ፍጡራኑ በአምልኮ ረገድ በፈጣሪ እና በፍጡር መካከል አማላጆችን በማድረጋቸው ሳቢያ ነው። ሁሉም ሃይማኖቶች ያለ አማላጅ በቀጥታ ፈጣሪን ለማምለክ የተስማሙ እስከሆኑ ድረስ ሁላችንም ራሳችንን በአንድ ፈጣሪ አምልኮ ዙሪያ አንድ ሆነን ነው የምናገኘው። ለሰው ልጅ መቀራረብ እና ወደ ስምምነት የመምጣት ቁልፉም ይሀው ነው።
"የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በእኛና በእናንተ መካከል ትክክል ወደ ሆነች ቃል ኑ፡፡ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ፣ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጎ ላይይዝ ነው፤ በላቸው፡፡ እምቢ ቢሉም፡- እኛ ሙስሊሞች መሆናችንን መስክሩ በሏቸው።" (ቁርኣን ምዕራፍ 3: 64)
6. ፈጣሪ አምላክ አንድ፣ ብቸኛ፣ የሁሉ መጠጊያ ነው፤ ሚስት ወይም ልጅን መያዝ ለበላይነቱና ለልቅናው የሚመጥን አይደለም፤ አልተወለደም አልወለደምም፤ ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም።
7. “የአምላክ ልጅ” የሚለው ቃል በጥሬ ትርጉሙ ፈፅሞ ጥቅም ላይ የሚውል አይደለም። ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም አምላክ ብዙዎቹን የተመረጡትን ባሪያዎቹን “የእግዚአብሔር ልጆች” በማለት ተናግሯልና። አይሁዶችም ቢሆኑ ፈጣሪ አንድ እንደሆነ እና በምንም መልኩ ወንድ ልጅም ሆነ ሚስት እንደሌለው ነበር የሚያምኑት። ስለዚህም "የእግዚአብሔር ልጅ" በሚለው ቃል የተፈለገው "አብዱላህ" ወይም "የአላህ ባሪያ" የሚለው ነው። ይሁን እንጅ ከሮማውያን ወይም ከግሪክ የመጡ አንዳንድ የክርስቶስ ተከታዮች ይህንን ቃል አላግባብ ጥቅም ላይ አዋሉት፤ ይህም በቅርሶቻቸው ውስጥ በእግዚአብሔርን አካል ለበስ አድርገው በመግለጽ ነው።
8. አላህ ብቻ ነው ፍጹም የሆነ ሙሉነት እና ፍጹም የሆነ ችሎታ ያለው። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ስለ እኛ ሲል መሞት አያስፈልገውም። ሕይወትን የሚሰጠውም ሆነ የሚወስደው እርሱ ብቻ ነው። ስለዚህም አልሞተም አልተነሳምም። ሁልጊዜም ጻድቃን አገልጋይ ባሪያዎቹን እንደሚከላከልላቸውና ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ሁሉ መልእክተኛውን ዒሳ ዓለይሂ ሰላምንም ከመገደልና ከስቅላት ጥበቃ ያደረገላቸውና ያዳናቸውም እርሱው ነው።
9. የዓለማቱ ጌታ ለፍጥረታቱ እናት ለልጆቿ ከምታዝነውም በላይ አዛኝ ነው፤ ወደ እርሱ በተመለሱና በፀፀት ምህረት በጠየቁ ቁጥር ይቅር ይላቸዋልም።
10. አደም ከተከለከሉት ዛፍ በመብላታቸው ንስሃቸውን ሲቀበላቸው አላህ ለሰው ልጆች ያስተማረው ትምህርት ከዓለማቱ ጌታ ለሰው ልጆች የተሰጠ የመጀመሪያው ይቅር ባይነት ነበር። ስለዚህ የውርስ ኃጢአት የሚባል ነገር የለም፤ ኀጢአትን ተሸካሚም ነፍስ የሌላዋን ሸክም አትሸከምም፤ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ጥፋት ብቻውን ይሸከማል፤ ይህ የዓለማቱ ጌታ ለእኛ ካለው እዝነት መካከል አንዱ ነው።
11. ይቅር ባይነት (ምህረት) ግን ከፍትህ ጋ የሚጋጭ ነገር አይደለም። ልክ ፍትህም ይቅር ባይነትን (ምህረትን) የሚከለክል እንዳልሆነው ሁሉ ማለት ነው።
12. የሰው ልጅ ያለ ኃጢአት ንጹሕ ሆኖ ነው የሚወለደው፤ ለሚፈፅመው ነገር የተጠያቂነት ኃላፊንቱ የሚጀምረውም ለአቅመ አዳም ወይም አዋቂነት ዕድሜ ከደረሰ ጀምሮ ነው።
13. ዓረብ በሆነውና ዓረብ ባልሆነው መካከል አላህን በመፍራት (ተቅዋ) እና በመልካም ስራ ካልሆነ በስተቀር ምንም ልዩነት በሌለው መልኩ ሰዎች አላህ ዘንድ እኩል ናቸው። ይህም የዓለማቱ ጌታ ርህራሄ፣ ፍትሃዊነት እና የመሳሰሉት መልካም ስምና ባህሪያቱን የሚያሳይ ነው። "እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፡፡ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፡፡ አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፡፡ አላህ ግልጽን ዐዋቂ ውስጥንም ዐዋቂ ነው።" (ቁርኣን ምዕራፍ 49: 13)
14. ከዓለማቱ ጌታ ባህሪያት አንዱ ጥበብ ነው፤ ምንም ነገር -ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር የበላይ የሆነው አላህ ጥራት ተገባው- ለከንቱ (ለቀልድ) አይፈጥርም። ይልቁኑ በጥበብና በዕውቀት ነው የሚፈጥረው። "ሰማይንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ ቀላጆች ሆነን አልፈጠርንም።" (ቁርኣን ምዕራፍ 21: 16)
15. የሰው ልጅ ልክ በእምነቱ እና በመልካም ሥራው ካልሆነ በቀር መዳንን እንደማያገኝ ሁሉ ባልሠራው ኃጢአትም አይጠየቅም። አላህ ለሰው ልጅ ሕይወትን፤ እንዲሁም ለፈተና እና ለመከራው የመምረጥ ነፃነትን ሰጥቶታል፤ ተጠያቂ የሚሆነውም ለድርጊቱ (ለሠራው ሥራ) ብቻ እንዲሆን አደረገው። በኦሪት ዘዳግም 24፡16 ላይ ተገልፆ እንደምናገኘው፦ "አባቶች ስለ ልጆቻቸው፣ ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ፤ እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል።" (ቁርኣን ምዕራፍ 35: 18 ይመልከቱ)
16. ይህ ሕይወት የመጨረሻ አይደለም፤ የበላይ የሆነው አላህ ሰውን የፈጠረው እንዲበላ፣ እንዲጠጣና እንዲራባ ብቻም አይደለም። አለበለዚያማ እንስሳት በዚህ ጉዳይ ከሰዎች ይሻላሉ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይራባሉና ለድርጊታቸው ግን ተጠያቂ አይሆኑም። አላህ ሰውን በምድር ላይ ባለው የተልዕኮ ኃላፊነት አክብሮታል፤ ከፈጠራቸው ብዙ ፍጥረታት መካከልም አስበልጦ አከብሮታል። ከዚያም በቀጣዩ ዓለም ለሠራው ሥራ ይመነዳዋል።
አላህን ይህ መጽሐፍ የቅኑ ጎዳና መመሪያ መብራት እንዲሆን እለምነዋለሁ።
በቅርቢቱም ሆነ በመጨረሻይቱ ዓለም ሕይወት በረካን እጠይቀዋለሁ።
Related books
All books
ለሰለሙ ጠቃሚ መመሪያ
በቁርኣን እና በነብያዊ ሓዲሥ በመጣው መሰረት ስለ ኢስላም አጠር ያለ መልዕክት።59 ቋንቋበቁርኣን እና በነብያዊ ሓዲሥ በመጣው መሰረት ስለ ኢስላም አጠር ያለ መልዕክት።
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው። እስልምና (ማስረጃ አልባ ቅጂ)[1] ለዚህ ፅሁፍ እያንዳንዱ ሃሳብ በተከበረው ቁርኣናዊ እና ነብያዊ ሐዲሥ ማስረጃ በተሟላ መልኩ ሌላ ቅጂ ያለ ሲሆን በተከታዩ ሊንክ ማግኘት ይችላሉ፦ https://islamhouse.com/ar/books/283007 አጠር ባለ መልኩ እስልምናን ስለ ማስተዋወቅ፣ ስለ አሳሳቢ መሰረቶቹ፣ ስለ አስተምህሮቱ እንዲሁም ስለ መልካምነቱ መሰረታዊ ምንጮቹ ከሆኑት ቅዱስ ቁርኣን እና ነብያዊ ሓዲሥ በመመርኮዝ የሚዳስስ አሳሳቢ ፅሁፍ ሲሆን፤ ፅሁፉ ሙስሊምንም ይሁን ከሙስሊም ውጭ ያለውን ለአቅመ ሃላፊነት (አዳም ወይም ሄዋን) የደረሰ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ የሚገኘውን በየትኛውም መስክም ሁኔታም የሚገኝን ሁሉ የሚመለከት ፅሁፍ ነው። 1. እስልምና ወደ ሰው ልጆች ሁሉ የተላከ ዘላለማዊ የሆነ አምላካዊ የአላህ መልዕክት ነው።
وجوب العمل بالسنة وكفر من أنكرها23 ቋንቋوجوب العمل بالسنة وكفر من أنكرها
رسالة لطيفة تبين أهمية الالتزام بسنة النبي محمد صلى الله عليه وسلم وبيان كفر من ينكرها. تبدأ بالتأكيد على أن مصادر التشريع الإسلامي تعتمد على القرآن الكريم وسنة النبي محمد صلى الله عليه وسلم وإجماع علماء الأمة. تشرح الرسالة كيف أن القرآن وسنة النبي متلازمان، وتؤكد على ضرورة اتباع السنة لفهم وتطبيق أحكام الشريعة. يُستدل فيها بآيات القرآن وأحاديث النبي العدنان وشهادات من الصحابة والتابعين، لإثبات حجية السنة وأهمية التمسك بها. تُختتم الرسالة بتذكير المسلمين بضرورة طاعة الرسول والابتعاد عن مخالفة سنته لتحقيق الهداية والرحمة من الله جل جلاله.
ስለ እስልምና አጭር ገለፃ፤ በተከበረው ቁርአን እና በነብያዊ ሐዲሥ በመጣበት መልኩ71 ቋንቋስለ እስልምና አጭር ገለፃ፤ በተከበረው ቁርአን እና በነብያዊ ሐዲሥ በመጣበት መልኩ
እስልምና ይህ እስልምናን አጠር ባለ መልኩ የሚያስተዋውቅና የሚዳስስ አሳሳቢ መጽሐፍ ነው። መሰረታዊ ምንጮች ከሆኑት ከቅዱስ ቁርአን እና ከነብያዊ ሐዲሥ በመመርኮዝ ስለ (እስልምና) አሳሳቢ መሰረቶቹ፣ ስለ አስተምህሮቱ እንዲሁም ስለ መልካምነቱ የሚዳስስ አሳሳቢ ፅሁፍ ሲሆን፤ ኪታቡ ሙስሊምንም ይሁን ከሙስሊም ውጭ ያለ፤ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ የሚገኝ፤ በየትኛውም መስክም ይሁን በየትኛውም ሁኔታ የሚገኝን ለአቅመ ሃላፊነት የደረሰን ሁሉ የሚመለከት አሳሳቢ ኪታብ ነው። (ከተከበረው ቁርአንና ከነብያዊ ፈለግ ማስረጃዎችን ያካተተ ቅጂ) 1- እስልምና ወደ ሰው ልጆች ሁሉ የተላከ የአላህ መልዕክት ነው። እንዲሁም ዘውታሪ የሆነ አምላካዊ የመጨረሻ መልዕክቱም ነው። እስልምና ወደ ሰው ልጆች ሁሉ የተላከ የአላህ መልዕክት ነው። ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦ {አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አላክንህም፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።} (ሰባእ፡ 28) ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦ {(ሙሐመድ ሆይ!)፡-…