Skip to content
777 ሐዲስ

የነብዊ ሐዲሶች ኢንሳይክሎፒዲያ

ውጤቶችን አጣራ

ከ777 27 ካርዶች

ማጣሪያዎችን አጥፋ
«እስልምና በአምስት መሰረቶች ተገነባ እነርሱም: 'ላ ኢላሃ ኢለሏህ ወአንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉህ' (ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ የለም፤ ሙሐመድም የአላህ ባሪያና መልክተኛ ናቸው።) ብሎ መመስከር፣ ሶላትን ማቋቋም፣ ዘካ መስጠት፣ በተከበረው የአሏህ ቤት ሐጅ ማድረግ እና የረመዷንን ወር መፆም ናቸው።»
ሶሒሕ ነው። ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
"ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ የለም ሙሐመድም የአላህ መልክተኛ ናቸው ብለው እስኪመሰክሩ፣ ሶላትን ቀጥ አድርገው እስኪሰግዱና ዘካን እስኪሰጡ ድረስ ሰዎችን እንድጋደል ታዝዣለሁ። ይህንን ከፈፀሙ በኢስላም ሐቅ ካልሆነ በቀር ደማቸውና ገንዘባቸውን ከኔ ጠብቀዋል። ሒሳባቸውም አላህ ዘንድ ነው።"
ሶሒሕ ነው። ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።
"የከለከልኳችሁን ነገር ራቁ፤ ካዘዝኳችሁም ነገር የቻላችሁትን ያህል ፈፅሙ! ከናንተ በፊት የነበሩትን ህዝቦች ያጠፋቸው ጥያቄ ማብዛታቸውና ነቢያቶቻቸውን መቃረናቸው ነው።"»
ሶሒሕ ነው። ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከፍ ካለውና ከጠራው አላህ ባወሩት (ሐዲሠል ቁድሲይ) አላህ እንዲህ ብሏል: "ባሮቼ ሆይ! እኔ በደልን በነፍሴ ላይ እርም አድርጌያለሁ! በመካከላችሁም እርም አድርጌዋለሁ! ስለሆነም አትበዳደሉ! ባሮቼ ሆይ! ከመራሁት በስተቀር ሁላችሁም ጠማማ ናችሁና ምራቻን ከኔ ጠይቁ እመራችኋለሁ! ባሮቼ ሆይ! ካበላሁት በስተቀር ሁላችሁም ረሀብተኞች ናችሁና መብልን ከኔ ጠይቁ እመግባችኋለሁ! ባሮቼ ሆይ! እኔ ካለበስኩት በስተቀር ሁላችሁም የታረዛችሁ ናችሁና ልብስን ከኔ ጠይቁ አለብሳችኋለሁ! ባሮቼ ሆይ! እናንተ በሌሊትም ሆነ በቀን ትሳሳታላችሁ። እኔ ደግሞ ሁሉንም ወንጀሎችን እምራለሁ። ስለሆነም ምህረትን ከኔ ፈልጉ እምራችኋለሁ! ባሮቼ ሆይ! እናንተ እኔን ጉዳትን ልትጎዱኝ አትችሉም። ጥቅምን ልትጠቅሙኝ ዘንድም አትችሉም። ባሮቼ ሆይ! ከመጀመሪያዎቻችሁ እስከመጨረሻዎቻችሁ ሰዎችም ጂኖችም ሁሉም ከናንተ መካከል እንደሚገኝ አንድ እጅግ አላህን ፈሪ ቀልብ ያለው ሰውዬ ቢሆኑ ይህ ከንግስናዬ አንዳችም አይጨምርም። ባሮቼ ሆይ! ከመጀመሪያዎቻችሁ እስከመጨረሻዎቻችሁ ሰዎችም ጂኖችም ሁሉም እንደ አንድ እጅግ ጠማማ ቀልብ ያለው ሰው ቢሆኑ ይህ ከንግስናዬ አንዳችም አይቀንስም። ባሮቼ ሆይ! ከመጀመሪያዎቻችሁ እስከመጨረሻዎቻችሁ ሰዎችም ጂኖችም በአንድ ሰፊ ሜዳ ላይ ቢቆሙና ቢጠይቁኝ ለእያንዳንዱም የጠየቀኝን ብሰጠው መርፌ ባህር የገባች ጊዜ እንደምትቀንሰው ያህል ካልሆነ በቀር ይህ (መስጠቴ) እኔ ዘንድ ካለው (ሀብት) ምንም አይቀንስም። ባሮቼ ሆይ! ይህቺ ስራችሁ ናት ለናንተ አስቀምጥላችኋለሁ ከዚያም እራሷን እመነዳችኋለሁ። ምንዳውን መልካም ሆኖ ያገኘ አላህን ያመስግን ፤ ከዛ ውጪ ሆኖ ያገኘ ግን ከነፍሱ በስተቀር ማንንም እንዳይወቅስ።"
ሶሒሕ ነው። ሙስሊም ዘግበውታል።
"አንዳችሁ ለነፍሱ የሚወደውን ነገር ለወንድሙ እስካልወደደ ድረስ አላመነም።"
ሶሒሕ ነው። ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።
"ሁሉም የሰው ልጅ መገጣጠሚያ አጥንቶች ምፅዋት አለባቸው። ፀሐይ በምትወጣበት ቀናት ሁሉ በሁለት ሰዎች መካከል ማስታረቅ ምፅዋት ነው፤ ሰውዬውን መጓጓዣው ላይ እንዲወጣ ማገዝ፣ እርሷ ላይ ማሸከም ወይም እቃውን እርሷ ላይ መጫን ምፅዋት ነው፤ መልካም ንግግር ምፅዋት ነው፤ ወደ ሶላት የምትራመዳት ሁሉም እርምጃ ምፅዋት ነው፤ ከመንገድ ላይ ቆሻሻን ማስወገድ ምፅዋት ነው።"
ሶሒሕ ነው። ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
"አላህ መልካም (ጥሩ) ነውና ከመልካም (ከጥሩ) በቀር አይቀበልም። አላህ መልክተኞችን ባዘዘበት ነገር አማኞችንም አዟል። አላህ እንዲህ ብሏል: {እናንተ መልክተኞች ሆይ! ከተፈቀዱት ምግቦች ብሉ። በጎ ስራንም ስሩ። እኔ የምትሰሩትን ሁሉ አዋቂ ነኝ።} እንዲህም ብሏል: {እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከነዚያ ከሰጠናችሁ ጣፋጮችን ብሉ።}" ቀጥለውም ጉዞ የሚያረዝም፣ ፀግሩ የተንጨባረረ፣ ፊቱንና ልብሱን አቧራ ያለበሰው አንድ ሰውዬ አወሱ። እጁን ወደ ሰማይ እየዘረጋ: "ጌታዬ ሆይ! ጌታዬ ሆይ! እያለ ይለምናል። ምግቡ ሐራም ነው። መጠጡ ሐራም ነው። ልብሱ ሐራም ነው። በሐራም ነው የተገነባው። እንዴት ለርሱ ዱዓው ተቀባይነት ይኖረዋል?" አሉ።»
ሶሒሕ ነው። ሙስሊም ዘግበውታል።
ከዕለታት አንድ ቀን የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ ሳለን ድንገት ልብሱ እጅግ በጣም ነጭ የሆነ፤ ፀጉሩ ደግሞ እጅግ በጣም ጥቁር የሆነ ሰውዬ ብቅ አለ። በሱ ላይ የጉዞ ምልክት አይታይበትም፤ ከኛ ውስጥም አንድም የሚያውቀው ሰው የለም፤ ወደ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ መጥቶ ተቀመጠ። ጉልበቱን ወደ ጉልበታቸው አስጠጋ፤ መዳፎቹንም በታፋዎቹ ላይ አደረገና "ሙሐመድ ሆይ! ስለ ኢስላም ንገረኝ!" አላቸው። የአላህ መልዕክተኛም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም "ኢስላም ማለት ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን ልትመሰክር፣ ሰላት ደንብና ስርዓቱን ጠብቀህ ልትሰግድ፣ ዘካን ልትሰጥ ፣ ረመዷንን ልትፆምና ወደርሱ መንገድን ከቻልክም የአላህን ቤት ልትጎበኝ ሐጅ ልታደርግ ነው።" አሉት። እሱም "እውነት አልክ!" አላቸው። "በሱ ተገረምን ይጠይቃቸዋልም (ጥያቄውን በትክክል እንደመለሱ) ያረጋግጥላቸዋልም።" ከዚያም፦ "ስለኢማን ንገሩኝ!" አላቸው። እሳቸውም "በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በጥሩውም ሆነ መጥፎ ውሳኔዎቹም ልታምን ነው።" አሉት። እሱም "እውነት አልክ!" አላቸው። "ስለኢሕሳን (በጎ መስራት) ንገሩኝ!" አላቸው። እሳቸውም "አላህን ልክ እንደምታየው ሆነህ ልትገዛው ነው። አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሀልና።" አሉት። "ስለ ሰዓቱቱ (ቂያማ) ንገረኝ!" አላቸው። እሳቸውም "ስለርሷ ተጠያቂው ከጠያቂው የበለጠ አዋቂ አይደለም።" አሉት። "ስለ ምልክቶቿ ይንገሩኝ!" አለ። እሳቸውም "ባሪያ ጌታዋን ልትወልድ ነው ፤ ያልተጫማ፣ የታረዘ፣ ድሃና የፍየል እረኛ የሆኑ ሰዎች ለህንፃዎች ሲሽቀዳደሙ ማየትህ ነው።" አሉት። ዑመር እንዲህ አለ "ከዚያም ሄደ። የተወሰነ ጊዜ ቆየሁ። ከዚያም ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም "ዑመር ሆይ! ጠያቂው ማን እንደነበር አውቀሀልን?" አሉኝ። እኔም "አላህና መልክተኛው ያውቃሉ።" አልኳቸው። እሳቸውም "እርሱ ጂብሪል ነው እምነታችሁን ሊያሳውቃችሁ መጥቷችሁ ነው።" አሉ።
ሶሒሕ ነው። ሙስሊም ዘግበውታል።